አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ


ሰኔ 24 /2013(ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል በተፈጠረ ሁኔታ የሰብዓዊ ተግባራት ለማሳለጥና የክረምት ወቅት በመሆኑ ማህበረሰቡን የእርሻ ሥራውን ተረጋግቶ እንዲያከናውን የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁን ተናግረዋል። ይህ የመንግሥት እርምጃ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ሲነሳ የነበረን ስጋት በመቅረፍና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት ሥራቸውን በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሰሩ ለማስቻል ሊረዳ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በኢትዮጰያ ለሰብአዊ ድጋፍ ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነው፣ ይሄው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል::

ኢትዮጵያ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መካሄዷን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅትም የምርጫ ውጤቱ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በውይይታቸው ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በብዙ ዘርፎች ከማጠናከር ጎን ለጎን በባለብዙ መድረኮችም መደጋገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን አቶ ደመቀ ሀሳብ አቅርበዋል።

የደቡብ ኮሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቹንግ ኢዩ ዮንግ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነትን በማስቀደም በተናጥል ያወጀውን የተኩስ ማቆም ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ምርጫ በሰላማዊ ሁኔታ በመጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አክለውም ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በአለም አቀፍ መድረኮችም በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደቡብ ኮሪያ እ.ኤ.አ ታህሳስ 2021 በምታስተናግደው የUNPKO(United Nations Peace Keeping Operations) ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እንድትሳተፍ የቀረበውን ግብዣ መቀበላቸውን ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።