ሰኔ 15/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለሁለት ቀናት በተባበሩት አረብ ኤመሬትስ በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው መክረዋል።
የሁለቱ ሃገራትን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንዲሁም በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች ሃገራቱ በሚኖራቸው ትብብር ዙሪያ መወያየታቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በተባበሩት አረብ ኤመሬትስ የነበራቸውን የስራ ተልዕኮ በማጠናቀቅ በዛሬው ወደ ሞስኮ – ሩሲያ አቅንተዋል ተብሏል።
አቶ ደመቀ ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
በሞስኮ በሚኖራቸው የስራ ቆይታ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማስረዳት እና በሃገራቱ መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች የበለጠ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።