አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጥሪ አቀረቡ

ነሐሴ 7/2016 (አዲስ ዋልታ) የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ጊዜው ያለፈበት አሰራሩን እንዲያሻሻልና ለአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲሰጣት ጥሪ አቀረቡ።

ዋና ጸኃፊው ትናንት “ሰላም እና የጸጥታን ማፅናት፤ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነትን መፍታት እና በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ውጤታማ ውክልና ማሳደግ” በሚል ርዕስ የምክር ቤቱ ክርክር ላይ ባቀረቡት ሃሳብ አሁን ያለው የምክር ቤቱ አሰራርና በአባላት ስብጥሩ በፍጥነት ከሚለዋወጠው የዓለም ስርዓት ጋር እኩል የሚራመድ አይደለም ብለዋል።

ምክር ቤቱ ለዓለም ሰላምና ጸጥታ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ያሰሠሩት ዋና ጸኃፊው ከመሰረቱ ሊካድ የማይቻል ትልቅ ስንጥቅ አለበት ብለዋል።

የዓለም ቀዳሚው የሰላም እና የፀጥታ አካል ከአንድ ቢሊዮን በላይ ህዝብ ላላት አፍሪካ አህጉር ቋሚ ድምጽ አለመኖር ልንቀበለው የምንችለው ጉዳይ አይደለም ሲሉም አክለዋል።

ተቋሙ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በአሸናፊዎቹ አገራት ሲቋቋም በቅኝ ግዛት የሚማቅቁት አፍሪካዊያን በወቅቱ ምንም ዓይነት ድምፅ አልነበራቸውም ሲሉም አመልክተዋል።

በግጭት፣ በቀውስ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በእዳ ጫና የምትማቅቀው አፍሪካ እንደ ጸጥታው ምክር ቤትና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች በመሳሰሉ ተቋማት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንደሌላትም ዋና ጸኃፊው አንስተዋል።

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በንግግራቸው “መልዕክቱ ግልፅ ነው፤ የአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ የሌለነበት የዓለም ሰላምና ጸጥታ ሊኖር አይችልም” ማለታቸውን ከድርጅቱ የፕሬስ መግለጫ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ዋና ጸኃፊው ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ ሁሉንም አገራት የሚወክል የዓለም የሰላምና ጸጥታ ተቋም እንዲኖር ሁሉም የድርጅቱ አባል አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።