አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ህወሓትን በማዳን ስራ ላይ መጠመዳቸው ተጠቆመ

ላውረንስ ፍሪማን

ጥቅምት 17/2015 (ዋልታ) አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ኢትዮጵያ የተረጋጋች እንዳትሆን ህወሓትን በማዳን ስራ ላይ መጠመዳቸውን አሜሪካዊው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በምትከተለው ስኬታማ ፖሊሲና ባላት የመልማት እምቅ አቅም የተነሳ ከአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና ድርጅቶች ተደጋጋሚ ጫናዎች እየደረሰባት መሆኑን ገልጸዋል።

አሜሪካዊው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የተወሰኑ ምዕራባውያን አፍሪካን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው እንደፈለጉ የማዘዝ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው።

በአህጉሪቱ ጠንካራ መንግስትና ሀገር እንዳይኖር እየሰሩ ስለመሆኑ ጠቁመው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በማባባስ ደካማ ሀገር የመፍጠር እቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በቅርቡ መንግስት የሀገር ሉዓላዊነትን ለማጽናት በትግራይ ክልል ቁልፍ ከተሞችን እየተቆጣጣረ ሲመጣ ምዕራባውያኑ በመንግስት ኃላፊዎቻቸው፣ በተቋማትና በሚዲያዎቻቸው ጭምር ጫና እያሳደሩ ያሉትም ለዚሁ ነው ብለዋል።

በእነዚሁ አካላት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ለእነሱ የሚላላክ መንግስት ለመፍጠር ካላቸው የረጅም ጊዜ እቅድ የሚቀዳ ስለመሆኑም ተንታኙ ገልጸዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የተጣለባቸውን ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለህወሓት ድጋፍ ሲያደርጉ ምዕራባውያኑ በዝምታ የሚያልፉት ከጀርባ ካላቸው ድብቅ ፍላጎት የተነሳ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ አንዳንድ ምዕራባውያን የሰሜኑን ጦርነት በፍርደ ገምድል ውሳኔያቸው የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ግፍ የተፈጸመባቸውን ሚሊዮን ዜጎች መዘንጋታቸው አሳዛኝ መሆኑን ተናግረዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት እና ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች መጀመሪያ ለሀገሪቱ አዲስ አስተዳደር ሲያደርጉት የነበረው ድጋፍ ቢቀጥል ኖሮ አሁን በኢትዮጵያ የተከሰቱት ችግሮች ሁሉ አይፈጠሩም ነበር ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የእነዚህ አካላትን የረጅም ዓመታት ሴራ በአግባቡ መገንዘብና አንድነትን በማጠናከር የህወሓትን ጉዳይ በማንኛውም አማራጭ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት አለበት ሲሉም አክለዋል።