አንድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በምክክርና በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ግንቦት 29/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) አንድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በምክክርና በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃፊዎች ጋር እያካሄደ ባለው የትውውቅ መርኃ ግብር ላይ ነው።

በመድረኩ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከአማራ ክልል የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች እና ወጣቶችም ተሳታፊ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል  ❝አንድ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ችግሮቻችንን በምክክርና በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል❞ ብለዋል።

ልዩነታችንን በማጥበብና በመቻቻል የተመሰረተች ጠንካራ ሀገር እንድትኖረን የአማራ ክልል መንግሥት ከሀገራዊ ምክክሩ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚለያዩንን አጀንዳዎች ለመቀነስ እና አንድነትን ለማጠናከር አልሞ የተቋቋመ ነው ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።