አኩሪ ድል ላስመዘገቡት አትሌቶች እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሸልማት ተበረከተ

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡ አትሌቶች ከ50 ሺሕ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሸልማት ተበረከተ፡፡

በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመዘገበውን አኩሪ ድል በማስመልከት የአትሌቶች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል መርኃ ግብር በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት እየተካሄደ ነው፡፡

በመርኃ ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አኩሪ ድል ላስመዘገቡ አትሌቶች እና ሌሎች የልዑካን ቡድን አባላት ከ50 ሺህ ብር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

በሻምፒዮናው ለተሰንበት ግደይ በ10 ሺሕ ሜትር የመጀመሪያውን ወርቅ በማስገኘቷ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር እና በ5 ሺሕ ሜርት ላሳየችው ውጤታማ የቡድን ሥራ 500 ሺሕ ብር በድምሩ የ2 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በተጨማሪም በሴቶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘችው አትሌት ጎይተቶም ገብረ ሥላሤ እና በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ታምራት ቶላ እያንዳንዳቸው የ1 ሚሊየን 750 ሺሕ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

እንደኤፍቢሲ ዘገባ በ1 ሺሕ 500 ሜትር የብር ሜዳሊያ እና በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘቸው ጉዳፍ ጸጋይ በልዩ ሁኔታ የ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በወንዶች ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ ያስገኘው ሞስነት ገረመው 1 ሚሊየን ብር፣ በ3 ሺሕ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያስገኘቸው ወርቅውሃ ጌታቸው 1 ሚሊየን ብር እንዲሁም በ3 ሺሕ መሰናክል የብር ሜዳሊያ ላስገኘው ለሜቻ ግርማ የ1 ሚሊየን ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡