አካል ጉዳተኞች አዲስ ከሚመሰረተው መንግስት የተሻለ እንደሚጠብቁ ገለጹ

መስከረም 23/2014 (ዋልታ) – አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ከቀደመው የተሻለ ትኩረት እንዲያገኝ እንደሚሹ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገለጹ።

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ አዲሱ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብት ማክበር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን ብሏል።

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አካል ጉዳተኞች አዲሱ መንግሥት በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ መስኮች በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ መመዘኛ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንዲያደርጉ ይፈልጋሉ።

አካል ጉዳተኞች የመሪነት ሚና እንዲኖራቸውና በሀገር ግንባታ ድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል ከአዲሱ መንግስት የምንጠብቀው ተግባር ነው ብለዋል።

አካል ጉዳተኞች መስራት የሚችሉ ዕውቀትና አቅም ያላቸው መሆኑን አምኖ የሚቀበልና በትክክል የሚያሳትፍ መንግሥት መሆን አለበት ያሉት አቶ ዓባይነህ፤ የአካል ጉዳተኞች ሕግ አንዲወጣ እንፈልጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ከተወዳደሩት 99 የአካል ጉዳተኞች መካከል 66ቱ ማሸነፋቸውንም ገልጸዋል።

አዲሱ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብትን በማክበርና ማስከበር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ያስተካክላል ብለን እንጠብቃለን ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር እርግብ ገብረሃዋርያ ናቸው።

በአገሪቷ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ አይደሉም ያሉት ኮሚሽነሯ፣ መንግሥት በቀጣይነት በዘርፉ በሚያከናውናቸው ተግባራት ችግሩን መፍታት አለበት ብለዋል።

በዚህም የአካል ጉዳተኞችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይረጋገጣል የሚል ተስፋና እምነት ከአዲሱ መንግሥት እንደሚጠብቁ ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

አዲስ የሚዋቀረው ካቢኔ የፍትህ ሥርዓቱን ማጠናከርና ተቋማት መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራ ትልቅ የህዝብ ተቀባይነት እንደሚኖረውም በአስተያየታቸው አመልክተዋል፡፡