አካባቢያችን የሸኔ መደበቂያ እንዳይሆን ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን – የሀሮሠቦ ከተማ ነዋሪዎች

ሐምሌ 2/2014 (ዋልታ) አካባቢያችን የሸኔም ሆነ የሌላ አሸባሪ አካል መደበቂያ እንዳይሆን ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን ሲሉ የሀሮሠቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን በዳሌሠዲ ወረዳ የሀሮሠቦ ከተማ ነዋሪዎች ከመከላከያ ሠራዊት አመራር ጋር በአካባቢው ሠላምና ፀጥታ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱም የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳው አስተዳደር፣ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ተገኝተዋል።

በስፍራው ግዳጅ እየፈፀመ ያለው የክፍለ ጦር አዛዥ ብ/ጀኔራል ተክሉ ሁሪሣ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የአካባቢያችሁን ሠላምና ፀጥታ ከሚያውኩ አሸባሪ ኃይሎች በንቃት ለመጠበቅ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጋር በቅንጅት መስራት አለባችሁ ብለዋል።

የውጭ ጠላቶቻችን ተላላኪ ሆነው ሀገር ለማፍረስ የተሰለፉ እንደ ሸኔ ያሉ ጥርቅም አሸባሪዎችን ለመደምሰስ የሁላችንም ተሣትፎ ያስፈልጋል ያሉት የክፍለ ጦሩ አዛዥ የዚህ ዓላማቢስ አሸባሪ ኃይል ተሳታፊን ለይቶ ለህግ መጠቆም የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የሀሮሠቦ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያችን ሠላም እንዲሆን እንፈልጋለን፤ የተጀመረውን ዘመቻ ከመንግሥት ጎን በመሆን ወረዳችን የሸኔም ሆነ የሌላ አሸባሪ አካል መደበቂያ እንዳይሆን ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን ሲሉ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW