አዋሽ ባንክ የስራ ፈጠራ ውድድር አስጀመረ

ግንቦት 8/2014 (ዋልታ) አዋሽ ባንክ “ታታሪዎቹ” የተሰኘ የስራ ፈጠራ ውድድር አስጀምሯል፡፡

ባንኩ የስራ ፈጠራ ሃሳብ ይዘው ለሚመጡ ስራ ፈጣሪዎች የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሙያ ክህሎት ስልጠና ላይ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጎ ይሰራልም ተብሏል፡፡

“ታታሪዎቹ” የስራ ፈጠራ ውድድርም የስራ ፈጠራ ሃሳብ ኖሯቸው በፋይናንስ እጥረት ተግባራዊ ማድረግ ላልቻሉ የስራ ፈጣሪዎች ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ጸሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡

ውድድሩ በዋናነት የክህሎት ስልጠና፣ መነሻ ካፒታልና ዘላቂ ብድር የሚመቻችበት መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር 1 ሺህ እጩዎችን በመቀበል በተዘጋጁ የስልጠና ማዕከላት የክህሎት ስልጠና በመስጠት የሚጀመር ሲሆን 100 ሰልጣኞች ባቀረቡት የስራ ፈጠራ ሃሳብ ተመዝነው ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉ ይሆናል፡፡

በመቀጠልም ተጨማሪ ስልጠና ከተሰጣቸው በኃላ በዳኞች ምርጫ 10 የስራ ፈጠራዎች ይለያሉ፡፡

በመጨረሻው ዙርም ዳኞች 5 ተወዳዳሪዎችን በመምረጥ ከ5ቱ ተወዳዳሪዎች 1ኛ ለሚወጣው አሸናፊ የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማትና፣ የ5 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ብድር እንደሚመቻች ፕሬዝደንቱ አስታውቀዋል፡፡

ተወዳዳሪዎች የመወዳደሪያ የስራ ፈጠራ ሃሳባቸውን በእንግሊዘኛ፣ አማርኛና አፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ማመልከት እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን በባንኩ ድረ ገፅ ወይንም በአካል ማመልከት ይችላሉ፡፡

በውድድር ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ተገኝተዋል፡፡

በሳሙዔል ሓጎስ