አየር መንገዱ በሎጂስቲክስ ዘርፍ የላቀ ሰርተፍኬት ሽልማትን ተቀበለ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ኢንዳስትሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም ዐቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አያታ) በሎጂስቲክስ ዘርፍ የላቀ የሰርተፍኬት ሽልማትን ተቀበለ።
አየር መንገዱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫው እንዳስታወቀው ከማኅበሩ የተበረከተለት ይህ የላቀ የምስክር ወረቀት ሽልማት ከአፍሪካ የመጀመሪያው ያደርገዋል።
ሽልማቱ በብራስልስ፣ ሻንጋይ፣ ጆሃንስበርግ፣ ፓሪስ፣ ሴኡል፣ ሌጎስ፣ ሉሳካ፣ ቤጂንግ፣ ሆንግኮንግን ጨምሮ ማስትሪችት፣ ቺካጎ እና አዲስ አበባ የሚደረገውን የአቅርቦት ግብ የበለጠ የሚያሻሽል ሲሆን ቀልጣፋ እና ውጤታማ የህክምና ዘርፍ (ፋርማሲዩቲካል) ማጓጓዣ እንዲኖር ያደርጋልም ብሏል አየር መንገዱ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም “ይህን ጠቃሚ ዓለም ዐቀፍ የምስክር ወረቀት በማግኘታችን በጣም ደስተኞች ነን” ብለዋል።