አየር መንገዱ ቦይንግ 777-8 የጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላን ለመግዛት ስምምነት ተፈራረመ

የካቲት 26/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 777-8 አዲስ የጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላን ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ከቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱ አየር መንገዱን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እያደገ ከመጣው የካርጎ ጭነት አገልግሎት ፍላጎት ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግና እያስመዘገበ የሚገኘውን ዕድገትም ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረማርያም “በአፍሪካ አቪየሽን መስክ ቀዳሚ አየር መንገድ እንደመሆናችን መጠን ይህንን አዲስ፣ ዘመናዊና ነዳጅ ቆጣቢ የጭነት አውሮፕላን ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረማችን ደስታ ይሰማናል” ብለዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እያደገ የመጣውን የአየር መንገዱን የካርጎ ጭነት አገልግሎት በማስፋፋት አሁን ያሉትን 66 ዓለም ዐቀፍ መዳረሻዎች ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳዋል ማለታቸውን ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።