አየር ኃይሉ፤ ኢትዮጵያ ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል- ሌ/ጀኔራል ይልማ መርዳሳ

ነሐሴ 23/2014 ዋልታ አየር ኃይሉ መክፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍሎ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡

አየር ኃይሉ አካዳሚ በኤሌክትሮኒክስ፣ በአውሮፕላን አካል እና ሞተር ጥገና እንዲሁም በመሰረታዊ የአቪዬሽን ሙያ ያሰለጠናቸውን የሰራዊት አባላት አስመርቋል።

በምርቃ ስነ -ስርዓቱ ላይ ተገኝተው በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ሰልጣኞች ሰርተፍኬትና የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት መልዕክት ያስተላለፉት ሌተናል ጀኔራል ይልማ፤ አየር ኃይሉ ከሀገራዊ ለውጡና ከተቋማዊ ሪፎርሙ በኋላ የዝግጁነት አቅሙን ለማሳዳግ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በዘመናዊ ትጥቆች እና ቴክኖሎጂ ብሎም ሰፋፊ የውጊያ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት በትኩረት መስራት መቻሉን ገልፀዋል።

“ተመራቂዎች ያለንበትን ወቅት በመረዳትና የተማራችሁትን ሙያ ወደ ተግባር በመቀየር ሀገራዊ ግዴታችሁን መወጣት አለባችሁ” ሲሉ አሳስበዋል።

አየር ኃይላችን መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ለማድረግ በላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ሲሉም አረጋግጠዋል ።

ለታላቅ ሀገር ታላቅ ተቋም በመገንባት ብሎም ብቃትና ጥራት ያላቸውን ባለሙያዎችን በማፍራትና የኢትዮጵያን ጠላቶች ድባቅ በመምታት አየር ኃይሉ የጀግኖች መፍለቂያ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ እንደሚገኝም ዋና አዛዡ ተናግረዋል ።

የኢፌዲሪ አየር ኃይል አካዳሚ አዛዥ ኮ/ል ገዛኸኝ ነጋሽ በበኩላቸው በአስተሳሰብና ክህሎት ብቁ የሆነ የሰው ኃይል በመፍጠር ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀት መሸከም የሚችል ፓይለትና ቴክኒሽያን እንዲሁም ሌሎች ሙያተኞችን በማፍራት በአካዳሚው በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

በቀጣይም ኮሌጁን በቴክኖሎጂ ይበልጥ በማዘመን ከአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ተቋም ለማድረግ በትጋት እየሰራን እንገኛለን ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።