አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ

ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር)

ሚያዝያ 3/2015 (ዋልታ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ለመሆን የሚያስችሉት ዝግጅቶች ማጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) አስታወቁ።

የዩኒቨርሲቲዎች “ራስ ገዝ” መሆን የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነጻነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በትምህርት ሚኒስቴር መገለጹ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) ዩኒቨርሲቲው ሲመሰረት ራስ ገዝ እንደነበር አስታውሰው በተለያዩ ምክንያቶች ራስ ገዝነቱን አጥቶ መቆየቱን ገልጸዋል።

ከረዥም ዓመታት በኋላ እንደገና ራስ ገዝነቱን እውን ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲዎችን የኢኮኖሚና አስተዳደራዊ ነፃነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቶ ማጠናቀቁን ፕሬዝዳንቱ ይፋ አድርገዋል።

የፋይናንስና የሰው ኃይል አደረጃጀት መመሪያ ተዘጋጀቶ ከሠራተኞች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰው መመሪያው በቀጣይ ለቦርድ ውሳኔ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን የዝግጅት ሥራውን አጠናቆ የአዋጁን መጽደቅ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ላይ በ14 ካምፓሶች 70 የቅድመ ምረቃ እና 293 የድህረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራሞችን እየሰጠ ይገኛል።

በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የምርምር ተልዕኮ የተሰጣቸው እና የመጀመሪያው ትውልድ ተብለው የተለዩ አሥር ዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።