ጥር 9/2015 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጨማሪ አዲስ የደንብ ልብስ ስራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ስትራቴጂክ ዕቅዱን መሰረት በማድረግ ልዩ ልዩ አዳዲስ የደንብ ልብሶችን አስመርቆ እየተገለገለ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡
ተቋሙ ከዚህ ቀደም ለተወርዋሪ ኃይል ሲጠቀምበት ከነበረው የደንብ ልብስ በተጨማሪ ከጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ የደንብ ልብስ ስራ ላይ እንደሚያውል በአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ም/ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡
የደንብ ልብስ በተሻለ መልኩ ጥራቱን ጠብቆ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ም/ኮማንደር ማርቆስ ህብረተሰቡን እና ባለድርሻ አካለት ይህንን የደንብ ልብስ የለበሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮችና አባላት መሆናቸውን ተገንዝበው ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ መገልገል ሆኖ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን አስታውሰው የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ የሚገለገሉም ሆነ አመሳስለው የሚጠቀሙ አካላት ከህገወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ መሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የፖሊስ ተቋማትን ለማዘመን በተያዘው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መሰረት የፖሊስ ሰራዊት አርማ እና የደንብ ልብስ እንዲቀየር መደረጉ ይታወቃል፡፡