አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ለህዳሴ ግድብ ከ1.8 ሚለየን ብር በላይ በስጦታ አበረከተ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ1 ነጥብ 8 ሚለየን ብር በላይ በስጦታ አበረከተ።

ባንኩ ደንበኞቹ ከውጭ ሀዋላ አገልግሎትና ከውጭ ሃገር ገንዘብ ግዥ የሰበሰበውን ከአንድ ሚሊየን ብር ላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበርያ ፅህፈት ቤት  በስጦታ አስረክቧል።

ስጦታውን የተረከቡት የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ የህዳሴ ግድብ ሀገር አሻጋሪና ሃገሪቱ አሁን ካለችበት ኋላቀር ሂደት ወደ ተደራጀና ወደ በለፀገ ማህበረሰብ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን በመግለፅ እንደ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ያሉ ተቋማት ግድቡ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸው የሚበረታታ እንደሆነ አንስተዋል።

አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ በ6 ወራት ውስጥ የሰበሰበውን ገንዘብ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ማዋሉን በመግለፅ ከዚህ ቀደም ለሸገር ፕሮጀክት፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለገበታ ለሀገር እንዲሁም ለተለያዩ ሀገራዊ ጥሪ ማህበራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

(በዙፋን አምባቸው)