አዲስ የዩኒቨርስቲ ገቢ ተማሪዎች እስከ ግንቦት 30/2013 ዓ.ም በየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ይጠራሉ- ሚኒስቴሩ

ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶየሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ 

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – የ2013 ትምህርት ዘመን አዲስ ዩኒቨርስቲ ገቢ ተማሪዎች እስከ ግንቦት 30/2013 ዓ.ም በየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንደሚጠሩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ በሰጡት መግለጫ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከተፈተኑ 343 ሺህ 832 ተማሪዎች 147 ሺህ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ተቋም የሚያስገባቸውን ውጤት ማምጣታቸውን አስታውሰው፣ በተፈጠረው የቅሬታ ማቅረቢያ ድህረ ገጽ እና በአካል  23 ሺህ 71 ቅሬታዎች ለሚኒስቴሩ እንደቀረበ ተናግረዋል፡፡

386 ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ተምረው በማህበራዊ ሳይንስና በማህበራዊ ሳይንስ ተምረው በተፈጥሮ ሳይንስ የተመደቡ መሆናቸውን በቅሬታ ማቅረባቸውንና ቅሬታው በሚኒስቴሩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮ ለመለየት የተሰራው ስራ አካል በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መስተካከሉን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የጤና ችግር እንዳላቸው ማስረጃ ያቀረቡ፣ ተመሳሳይ ጻታ ያላቸው መንትያዎች፣ ነፍሰጡርና ከሁለት አመት በታች ያሉ ህጻናት ያሏቸው ሴቶች፣ በስህተት ሴት ሆነው በወንድ ወይም ወንድ ሆነው በሴት ስም የተመዘገቡ ተማሪዎች፣ አይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸው እና አካል ጉዳተኞች አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ታይቶ በአጠቃላይ 1ሺህ 891 ቅሬታዎች ምላሽ ማግኘቱን ሚኒስቴሩ አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የተመደቡበት ተቋም ከመኖሪያ አካባቢያቸው ባለው ርቀት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በህክምና ማስረጃ ባልቀረበበት የጤና ችግር እና የሃሰተኛ ማስረጃዎች የቀረቡ ቅሬታዎች በተለያዩ መንገዶች ተጣርተው ተማሪዎች ከዚህ ቀደም በተመደቡበት እንዲማሩ ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

ሚኒስትሩ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ወስደው ቅሬታ ያቀረቡ ተማሪዎች ዳግም ምደባ ከሰኞ ግንቦት 16 ቀን ጀምሮ በበይነ መረብ ማየት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሰረት ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቀው አዲስ ገቢ ተማሪዎችን እስከ ግንቦት 30/2013 ዓ.ም ቅበላ እንደሚያደርጉና ሰኔ አንድ የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ትምህርት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህ አመት ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ 100 (Top 100) ያስመዘገቡ 206 ሴትና ወንድ ተማሪዎች የማበረታቻ ስርአት የተዘረጋ ሲሆን፣ በዚህም በአንደኛ ደረጃ በመረጡበት ትምህርት መስመር፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ ዲፓርትመንት እንዲማሩ እንደሚደረግና ተጨማሪ የትምህርት እድል እንዲያገኙ እንደሚሰራ አክለዋል፡፡

ይህ  እድል በቀጣይ አመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡