“የማዕድን ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል የማዕድን ኤግዚቢሽን እና ፎረም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው

ጥር 16/2014 (ዋልታ) “የማዕድን ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ቃል የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ እና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የክልሉ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የማዕድን ኤግዚቢሽን እና ፎረም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ማዕድን ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል የተፈጥሮ ሀብት ቢሆንም በሀገሪቱ ለረጅም ዘመናት ሳይንሳዊ ምርምሮችን በማድረግ በሚፈለገው መልኩ ሀብቱን ሥራ ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ተገልጿል።
የኦሮሚያ የማዕድን ሀብት ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ለሥራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በፎረሙ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ “ማዕድን ምድራችንን የሞላ የተፈጠሮ ሀብት ነው፤ ቢሆንም ይህን የተፈጠሮ ስጦታ በአግባቡ ተጠቅመን የሥራ አጥነት ችግሮችን መቅረፍ ሲገባን ትኩረት ሳንሰጠው በመቅረታችን ከሀብቱ ልናገኘው የሚገባንን ያህል ጥቅም አላገኘንም” ብለዋል።
አሁን ግን በየደረጃው ያለው አመራር ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ይህን የማዕድን ጎተራ ከፍተን የወጪ ንግድን በመጨመር የሀገራችንን ምጣኔ ሃብት ማሳደግ ይጠበቅብናል ሲሉም መናገራቸውን ከክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ ጉዳዩን በማስመልከት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ በኦሮሚያ የማዕድን ኤግዚብሽን እና ፎረም ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ኦሮሚያ የማዕድን ሀብት የተከማቸበት የማዕድን ጎተራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ጎተራውን በሁሉም መልኩ ተጠቅመን የሕዝባችንን ሕይወት ሊለወጥ፣ ሀገራችን ከሀብቱ ልትጠቀም ይገባል ብለዋል።
ኤግዚብሽኑ በማዕድን ዘርፍ ያለን ተስፋ ሰፊ እና ብሩህ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ እኛም በጥረታችን ተስፋው በተግባር እንዲገለጽ እናደርጋለን ሲሉም አክለዋል።