አገራቱ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

ሐምሌ 20/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ሩስያ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር ያለንን ታሪካዊ ግንኙነት በየጊዜው ስናሳድግ እንደመጣነው ሁሉ በዚህ ጉብኝትም በተለያዩ መድረኮች በጋራ ጉዳዮች ላይ ተደጋግፈን መስራት ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

ከውይይቱ በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫም ሚኒስትር ደመቀ በውይይታችን በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ያለንን ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ተስማምተናል ነው ያሉት።

የሕዳሴውን ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በተመለከተም ኢትዮጵያ በመርህ ተመስርቶ ፍሬያማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያላትን አቋም ገልጸውላቸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩስያ ባለፉት ሁለት ዓመታት መርህን እና እውነትን በመከተል ለኢትዮጵያ ላሳየችው ድጋፍ አመስግነዋል።

የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋራ ባላት ውጤታማ ግንኙነት ደስተኞች ነን ብለዋል።

የሁለቱ ሀገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ እንዲካሄድ ሩስያ ፍላጎቷ እንደሆነ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሰርጌ ላቭሮቭ አክለውም ሩስያ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።