አገር የማጥቃት ስህተታቸውን እንደቀልድ የሚነግሩን የዴሞክራሲ ሰባኪዎች

ታኅሣሥ 6/2014 (ዋልታ) ዴሞክራሲን ለመስበክ ከእኛ ወዲያ ላሳር የሚሉት አሜሪካ መራሽ አገራትና መገናኛ ብዙኃን አገር የሚያጠፋ ስህተት መፈፀማቸውን ለመረዳት እንኳን ዓመታትን ሲወስድባቸው ተመልክተናል፡፡
ለአብነት የአሜሪካው ተነባቢ ጋዜጣ ዘኒውዮርክ ታይምስ በኢራቅ ጦርነት ከባድ ስህተቶች መስራቱን በማመን አገር ያፈረሰውን ጦርነት በማራገብ በኩል የፈፀመውን ወንጀል ‹‹ስህተት ሰርተናል›› በሚል የአሜሪካ መንግሥት ብሂል ሲደግም እናስታውሳለን፡፡
ጋዜጣው በኢራቅ ጦርነት እንዲጀመር ማድረግን ጨምሮ የሰራቸውን ወንጀሎች በአዘጋጁ በኩል ከዓመታት በፊት መናዘዙ የሚታወስ ነው፡
ጋዜጣው በኢራቅ ጉዳይ ይጠቀማቸው የነበሩ ምንጮችን ተኣማኒነት መፈተሽን ጨምሮ ‹በአገሪቱ የሽብርተኞች ካምፕ አለ እንዲሁም ጅምላ ጨራሽ (አገር አውዳሚ) የጦር መሳሪያ ተከማችቷል የሚሉ› መረጃዎችን ያሰራጨበት መንገድ ስህተት እንደነበረበት ማተቱን ከዓመታት በፊት ዘጋርዲያን ይዞት የወጣውን ዘገባ ዛሬ ላይ ማንሳቱ ማስተማሪያ ይሆናል፡፡
ይሁንና ጋዜጣው ዛሬም ከስህተቱ ከመማር ይልቅ እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት ላይ ከዓመታት በኋላ እንደባለቤቶቹ የአሜሪካ መንግሥት ስህተት ሰርተን ነበር ሊል የሚችልበትን ወንጀል እየፈፀመ ይገኛል፡፡
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተስፈኛዋንና የነዳጅ ክምችቷ ከፍተኛ የሆነውን ሊቢያ በአማካሪዎቻቸው ተገፋፍተው በጦርነት ካመሳቀሏት በኋላ በሊቢያ ስህተት ፈፅመናል ማለታቸውን አይዘነጋም፡፡
የአሁኑ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ አገራቸው በሉኣላዊ አገር ላይ ዘላ ገብታ ለ20 ዓመታት የቆየችበትን የአፍጋኒስታን ጦርነት ይህን ያህል መቆየት አልነበረብንም በሚል አገሪቱንና ሕዝቧን አሸባሪ ብላ ለሰየመችው ታሊባን አስረክባ እንድትወጣ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ መሰረቱን ባደረገው ዴክላን ዋልሽ የተሰኘ ጸሐፊው በኩል የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት እንዳስገቧት አድርጎ ይከሳል፡፡
ጸሐፊው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ20 ዓመታት በውጥረት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ያደረጉት ለቀጣይ የጦርነት እቅዳቸው ጥርጊያ መንገድ ለማመቻቸት ነው ሲልም አይናችሁን ጨፍናችሁ ላሞኛችሁ ሲል የራሱን የምናብ ዓለም ፈጥሮ ይተርካል፡፡
መንግሥት ከራሱ መዋቅር ባሻገር በሃይማኖት አባቶች፣ በአገር ሽማግሌዎችና በሰላም እናቶች እንባም ጭምር ሕወሓት ወደጦርነት እንዳይገባና ሰላምን እንዲመርጥ ሲያስለምን የነበረበትን ጥረት ግን መረጃ ሰጪዎቹ ለኒውዮርክ ታይመስ ጸሐፊው አልነገሩትም ወይም ይህ መራራ ሃቅ እንዲታወስ አልተፈለገም።