አግልግሎቱ ባለፉት ስድስት ወራት 167 ሺሕ 850 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታወቀ

ሀብታሙ ታዬ

ጥር 15/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ደም እና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ባለፉት ስድስት ወራት 167 ሺሕ 850 ዩኒት ደም መሰብሰቡን አስታወቀ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአግልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ተቋሙ በስድስት ወራት 225 ሺሕ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ አቅዶ 167 ሺሕ 850 ዩኒት ደም በመሰብሰብ የዕቅዱን 75 በመቶ አፈጻጸም ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በደም ልገሳ ሂደት ላይ 61 በመቶ የሚሆኑት አዳዲስ ደም ለጋሾች መሆናቸውን ያመላከቱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መደበኛ የደም ለጋሾች እንዲኖሩ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መደበኛ በየሦስት ወሩ ደም የሚለግሱ ለጋሾች ቁጥር 10 በመቶ እንዲሆን ቢጠበቅም አሁን ላይ 3 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የደም ለጋሽ በጎ ፈቃደኞች በሚፈለገው ልክ አለመሳተፍ፣ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የትምህርት ቤቶች መዘጋት እና በክረምት ወቅት የለጋሾች መቀነስ ተግዳሮት ሆኖ መታየቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በበዓላት ወቅት ደም የመለገስ ሂደቱ አነስተኛ በመሆኑ በባንኮች ውስጥ እጥረት እንደሚያጋጥም የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ሰሞኑን በነበረው በዓላት በአንዳንድ ደም ባንኮች እጥረት እንዳጋጠመውም አስረድተዋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ 43 የደም ባንኮች እንዳሉት የጠቆሙት ኃላፊው አሁን ላይ በትግራይ ክልል ከሚገኙ ሦስት የደም ባንኮች ውጪ ሁሉም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ደም መስጠት ህይወት ማዳን በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የድርሻውን እንዲወጣ እና በየሦስት ወሩ ደም በመስጠት ሕይወትን እንዲያድን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው