አጣዬና አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚያሴሩ ኃይሎች

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) አጣዬና አካባቢው እንዳይረጋጋ የሚሰሩ አካላትን ከአሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ እኩል መታገል አለብን ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
የአጣዬ ከተማ ወጣቶች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአካባቢው ኮማንድ ፖስት፣ ከፌደራልና ከክልል የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አጣዬን መልሶ ለመገንባት ርብርብ እየተደረገ በመሆኑ ወጣቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደጉም ሚኒስትር ዴኤታው ጠይቀዋል፡፡
የአጣዬና አካባቢው ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ጀነራል ደስታ አብቼ ሕወሓት የሽብር ቡድን ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠር አገር ለመበተን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
እንደ ኢብኮ ዘገባ አሁን ላይ ይህ ቡድን ግብዓተ መሬቱ እየተፈፀመ ነው ያሉት ጀነራሉ፣ ሞቱን ለማፋጠን ወጣቶች መከላከያን በመቀላቀል ትግሉን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወጣቶቹ የከተማዋ መልሶ ግንባታ እንዲፋጠንና በከተማዋ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ የመከላከያ ሰራዊትን በመቀላቀል የኢትዮጵያን ጠላቶች ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡