አጣዬና አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ

ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ

ሚያዝያ 21/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በቅርቡ ተፈጥሮ የነበረው ችግር ተረጋግቶ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን የአካባቢው ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ አጥፊዎችን የመለየትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸው፣ ኮማንድ ፖስቱ ግዳጅ ከተሰጠው ጀምሮ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

ግጭትና ጸብ አጫሪነትን እንዲሁም መንገድ መዝጋትን በማስቆም የተቋረጡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ሥራዎች እንዲጀመሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደቀዬአቸው የመመለስና አጥፊዎችን ለይቶ ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራም ከኮማንድ ፖስቱ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በእነዚህ ላይ አተኩሮ በመሰራቱም በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ግጭትና የወንጀል ድርጊቶች መቆማቸውን ነው የተናገሩት።

አካባቢው የተረጋጋ እንቅስቃሴ እየታየበት መሆኑን ተከትሎም ተቋርጠው የነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የተቋረጡ የስልክ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችም ዳግም መጀመራቸውን የተናገሩት አስተባባሪው፣ አጥፊዎችን በፍጥነት የመለየትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ህዝቡ ሰላም ፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ከመንግስት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአካባቢው ተከስቶ በነበረው ችግር የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የመንግስት መዋቅር እጅ እንዳለበት መታወቁንና በቀጣይ በማስረጃ የተደገፉ መረጃዎች የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሰራ ሌተናል ጄኔራል ደስታ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።