“አፊኒ” – የሲዳማ ብሔር ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥነ ሥርዓት

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዘኃ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ እና ታሪክ ባለቤት ስትሆን በብዘኃነት ውስጥ ደግሞ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብና የወንድማማችነት ዕሴቶች ያሏት ድንቅና ውብ ሀገር ናት።

እነዚህን አብሮነት፣ መተሳሰብና ወንድማማችነትን በግለሰብ፣ በቤተሰብ እንዲሁም በቡድን መካከል የሚሸረሽር ግጭት ወይም አለመግባባት ቢፈጠር በባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ መፍትሄ ማበጀት የሚችሉ የሀገር በቀል ዕውቀቶች የኢትዮጵያ ህዝብ መለያዎች መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

በዛሬው የሀገሬ ዝግጅታችን በአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ የሲዳማ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ልናስቃኛችሁ ወደናል፡፡

በሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የባህል፣ ታሪክና ቅርስ ዳይሬክተር ተፈራ ሌዳሞ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሲዳማ ብሄር ከጥንት ጀምሮ በሰዎች ዕለታዊ ግንኙነት ሂደት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን የሚፈታበት ባህላዊ መንገድ እንዳለው ተናግረዋል።

ይህ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረና ለዘመናት ተጠብቆ የቆየው ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ “አፊኒ” ይባላል። ትርጉሙም “ሰማችሁ ወይ” ማለት መሆኑን ገልጸውልናል።

“አፊኒ” የሲዳማ ህዝብ ባህላዊ እሴቱና ለዘመናት ሲገለገልበት የቆየ የግጭት አፈታት ሥርዓት ሲሆን እድሜ፣ ፆታና ማኅበራዊ ደረጃን የማይለይ ሁሉንም አካታች መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በሲዳማ ባህል በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መካከል ግጭት ቢፈጠር ተጎጂው አካል አጠገቡ ላሉ ሰዎች አፊኒ (ሰማችሁ ወይ) ብሎ ስሞታውን ከገለፀ ግጭቱ ወዲያው ይቆማል።

የተበደለ ሰው ማንኛውንም አይነት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት “አፊኒ” በማለት የማሳወቅ ባህላዊ ግዴታ እንዳለውም ይገለጻል። በግብታዊነት እርምጃ የወሰደ አካል ቢኖር ደግሞ በአፊኒ ሥርዓት ቅጣት ይጣልበታል።

ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴው (አፊኒ) ከቤተሰብ ግጭት ጀምሮ ዛቻ እና ስድብ እንዲሁም እስከ ከባዱ ነፍስ ግድያ ላሉ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ ትልቅ የባህላዊ ዳኝነት መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

“አፊኒ” በዳይና ተበዳይን የመለየት ሥራ የሚሠራበት መንገድ ሲሆን ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት እሳቤው ከፍተኛ በመሆኑ በማህበረሰቡ ተቀባይነት እንዳለው ይጠቀሳል።

በአፊኒ የግጭት አፈታት ሥርዓት ለተበደለው ፍርድ የሚሰጠው በእውነት እና በጥበብ (ሀዮ እና ሃላሌ) በመሆኑ እርቁ የቀደመውን የማህበራዊ ግንኙነት በማስቀጠል ቤተሰባዊ ፍቅርና ወዳጅነት እንዲጠናከር የማድረግ ኃይል እንዳለውም ነው የተጠቆመው፡፡

ይህ የባህላዊ ዳኝነት የሚከናወነው በተናጠል ሳይሆን በሸንጎ ወይም በጉባኤ መሆኑን የሲዳማ አባቶች ያስረዳሉ።

“አፍኒ” ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ አራት ደረጃዎች እንዳሉት በቢሮው የባህል፣ ታሪክና ቅርስ ዳይሬክተር ተፈራ ሌዳሞ ነግሮናል።

የመጀመሪያው ቦሳሊ ሶንጎ የሚባል ሲሆን የተጋጨ ቤተሰብ ቢኖር ጉዳዩ ደጅ እንይወጣ በመስማማት በቤት ዙሪያ ግጭቱ የሚፈታበት የቤተሰብ ጉባኤ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ኡሉ ሶንጎ በመባል የሚታወቅ ነው። ከቤተሰብ አልፎ በጉርብትና እና በሰፈር ደረጃ የሚፈጠሩ ግጭቶች ሲከሰቱ የሚፈቱበት ነው።

ሦስተኛው ደግሞ አያዱ ሶንጎ የሚባለው ሲሆን በእርቅ ሥርዓት አንደኛው ወገን በውሣኔው ካልተስማማ ቅሬታ የሚያቀርብበት ወይም የሚያሰማበት እንደሆነ ይገለፃል።

አራተኛው የሽምግልና እርከን ሞተተ ሶንጎ ሲሆን ከበድ ያሉ ጥፋቶች እንዲሁም ከአካባቢው አልፎ ከጎሳ ውጭ ያሉ ግጭቶችን ጨምሮ የሚፈቱበት ሸንጎ ነው።

አፊኒ በእነዚህ በአራቱም ሂደቶች ጉዳዩ የሚመለከተው አካል በሸንጎ ፊት በነፃነት እንዲናገር ዕድል የሚሰጥ እንዲሁም በውይይትና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደትም አሳታፊ መሆኑ መለያው እንደሆነ ነው የገለጹት።

በሸንጎ ፊት ከቀረቡ አንደኛው ወገን የመቃወሚያ ሀሳብ ለማቅረብ ቢፈልግና “አፊኒ” ቢል ሀሳቡን እንዲያራምድ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ደግሞ ፍትሃዊነትን የሚያጎናጽፍ መሆኑ ይነገርለታል።

ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት እና በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላም እንዲሰፍን ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። በአቅራቢያቸው ፍርድ ቤቶች በሌሉባቸው ቦታዎች የበኩላቸውን ሚና ይወጣሉ።

ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ጊዜ፣ ወጪ እና እንግልትን በማስቀረት በኩል አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ነው በሲዳማ ክልል ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የባህል ታሪክ እና ቅርስ ዳይሬክተር ተፈራ ሌዳሞ የተናገሩት።

በሰው ልጆች ማህበራዊ ግንኙነት ከግል ወይም ከቡድን ፍላጎትና ጥቅም እንዲሁም ከሀሳብ ልዩነት የተነሣ ግጭት ሊከሰት ይችላል። በመሆኑም ግጭትን በማርገብ ብሎም በማስወገድ ረገድ ከመደበኛ የፍትህ ተቋማት አገልግሎት ባሻገር ማህበረሰቡ እንደ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ እና እምነት ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን መጠቀም ጉልህ ሚና እንዳለውም ይወሳል።

በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኙ ባህላዊ የግጭት አፈታትና ባህለዊ የዳኝነት ሥርዓቶች ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም ትውልዱ ለዘመናዊ ሥልጣኔ መሠረት የሆኑ የግጭት አፈታት ኢሴቶችና የሀገር በቀል ዕውቀቶችን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ተንከባክቦ የመጠቀም ኃላፊነት ይጠብቀዋል።
ቸር እንሰንብት!!

 

በሠራዊት ሸሎ