አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለ ግለሰብን በማገት ሊብሬውን በመቀየር መኪናውን ሊነጥቁ ነበር የተባሉ አምሥት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ።
የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች 1ኛ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣ 2ኛ የኡስታስ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ እና በአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ ልየው አሰፋ እና ዓለሙ ኦልጅራ ናቸው።
ክስ በቀረበበት ወቅት በክስ መዝገቡ በተራ ቁጥር 6 እና 7 ላይ ተጠቅሰው የነበሩት፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑን በሚመለከት በወቅቱ ታዘው በስራ ላይ ተመድበው እንደነበር ተጠቅሶ በተቋሞቻቸው ማረጋገጫ በመቅረቡ ምክንያት ነጻ መባላቸው ይታወሳል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሩት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ባቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ፤ ተከሳሾቹ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ የሆነውንና የዋጋ ግምቱ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጣ ቪ8 ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ማህደሩን በመለወጥና በሽያጭ በማስተላለፍ ለመውሰድ ሲሉ የተያዙ መሆኑ ተጠቅሷል፤ በዚህም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሰው ነበር፡፡
በዚሁ መሠረትም 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ወኪል በመሆን ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር የሆነውንና ከላይ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ አስቀድመው የተሽከርካሪውን መረጃ ለማግኘት ከ3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር “ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ” በሚል በግል ተበዳይ ስም ተመሳስሎ ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንደተሰጠ በማስመሰል በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እና ያላገባ የምስክር ወረቀት መጠቀሙ በክሱ ተመላክቷል።
በዚህ መልኩ በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት ሙሴ መረሳ ኃይሉ ለሚባል ግለሰብ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን ነኝ በሚል ውክልና መሰጠቱን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል።
በተሰጠው ውክልና ስልጣን መሰረትም ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በእጃቸው በሌለ ተሽከርካሪ የሽያጭ ውል እንዲፈፀም ካደረጉ በኋላ በ5ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በሕገ-ወጥ መልኩ ሊብሬ በማሰራት ንብረትነቱን ወደ 2ኛ ተከሳሽ እንዲዞር ማድረጋቸውም በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል።
ከዚህ በኋላም 1ኛ ተከሳሽ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ተሽከርካሪውን እየነዳ ባለበት ወቅት፤ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የድንገተኛ ስልክ ጥሪ ማዕከል 991 በመደወል መኪናው እንደተሰረቀበትና በመንገድ ላይ እየተነዳ እንዳየው በመግለፅ እንዲያዝለት በማመልከት የፌዴራል ፖሊስ ኢንተለጀንስ ሰራተኛ ከሆነው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በጋራ በመሆን መኪናውን አስቁመው እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ስራ በሚሰሩት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በሆኑ አካላት አማካኝነት ተሽከርካሪው እንዲያዝ በማድረግ እና በሀሰት ተሽከርካሪው ከዚህ በፊት የጠፋባቸው መሆኑን በመጥቀስ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ለቡ ፖሊስ ጣቢያ በማመልከት ግለሰቡ እንዲያዝ አድርገው ተሽከርካሪውን ሊወስዱ ሲሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በክሱ ተገልጿል።
3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጭ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር የግል ተበዳይን ተሽከርካሪ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም አስቀድሞ የዋጋ ግምት እንዲፃፍ በማድረግ እና ሽያጭ ተፈፅሟል በሚል ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ባለቤትነቱን ከግል ተበዳይ ከኡስታዝ አቡበከር ስም ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ካደረገ በኋላ፤ የግል ተበዳዩ በ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የተሽከርካሪ ቦሎ እድሳት ለማድረግ ወደ ተቋሙ በሄደበት ወቅት በሕገ-ወጥ የስም ዝውውር መደረጉንና ሀሰተኛ የተሽከርካሪው ሊብሬ በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዳለ እያወቀ ለግል ተበዳዩ ቦሎውን ያደሰለት መሆኑ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
4ኛ ተከሳሽ ደግሞ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዳታ ኢንኮደር ባለሙያ በመሆን ሲሰራ፤ ሰነድ ማጣራት እና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እያለበት ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ የባለቤትነት ስም መረጃውን ሳያጣራ እና ሳያረጋግጥ በሲስተም ላይ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አመላክቷል፡፡
5ኛ ተከሳሽም የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተሽከርካሪ ፈቃድ አገልግሎት ባለሙያ በመሆን በማገልገል ላይ እያለ፤ በስሙ ከንብረት ክፍል በወጣ ሊብሬ ሲስተም ላይ ሳይመዘገብ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ ባለቤትነት በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲሆን ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
ተከሳሾቹ ከላይ በተገለጸው ሁኔታ የቀረበባቸው የክስ ዝርዝር ከደረሳቸው በኋላ፤ የወንጀል ድርጊቱን አልፈጸምንም በማለት የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ የግል ተበዳዩን ኡስታዝ አቡበከርን ጨምሮ ሌሎችንም ምስክሮች አቅርቦ የምስክር ቃላቸውን በችሎት አሰምቷል፡፡
ፍርድ ቤቱም የምስክር ቃል መርምሮ ከ6ኛ እና ከ7 ኛ ተራ ቁጥር ከተጠቀሱ የፖሊስ አባላት ውጪ ያሉ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
በክስ መዝገቡ በተራ ቁጥር 6 እና 7 ላይ የተጠቀሱት ማለትም የአዲስ አበባ ፖሊስ የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና የፌደራል ፖሊስ የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑን በሚመለከት፤ በወቅቱ ታዘው በስራ ላይ ተመድበው እንደነበር ጠቅሶ ተቋሞቻቸው ማረጋገጫ በማቅረባቸው ምክንያት ነጻ ተብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ መርምሮና ከዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ጋር በማመዛዘን ዛሬ በነበረው የችሎት ቀጠሮ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ