ኢራን ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አምባሳደር ሶመድ አሊ ላኪዘዲ

የካቲት 9/2015 (ዋልታ) ኢራን ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ያለቅድመ ሁኔታ በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሶመድ አሊ ላኪዘዲ ኢትዮጵያ እና ኢራን ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው ግንኙነታቸውም በንግድ፣ ጸጥታ፣ ባህል እና ሌሎች ዘርፎች ተጠናክሮ መዝለቁን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ አገራት በግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ባህል፣ ፖለቲካ እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ከ20 በላይ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን የገለጹት አምባሳደሩ ወደፊትም አገራቸው በተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች ያላትን እምቅ ልምድ እና እውቀት ለማጋራት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡

ኢራን ከአፍሪካ አገራት ጋር ካላት የጠበቀ ሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በአፍሪካ ህብረት የታዛቢነት ወንበር እንዳላት ጠቁመው ከአገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡

የተለያዩ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ አገራት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ኢራን እንደምትቃወም ገልጸው አገራቸው የሌሎች አገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ አብራ እንደምትሰራም አመልክተዋል፡፡

በኤምባሲ ደረጃ ሁለቱ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1950ዎቹ እንደነበርም አምባሳደሩ አስታውሰዋል፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ