ኢትዮጵያ 2ኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት ስታከናውን የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም በማይነካ መልኩ ነው – አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ

ግንቦት 24/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሙሌት ሥራ ስታከናውን የተፋሰሱን ሃገራት ጥቅም በማይነካ መልኩ እንደሚፈፀም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤው የአሜሪካ ኮንግረሰ ሴናተር አባል ከሆኑት ጀምስ ኢንሆፌን ጋር በቀጣናዊና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ በህዳሴ ግድብ፣ በህግ ማስከበር፣ በሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት፣ ከሱዳን ድንበር ማስከበር ሥራ ጋር ተያይዞ ያለበትን ደረጃ እና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ላይ ለሴናተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት አፈ ጉባዔው፣ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችም ድጋፍ በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሱዳን ድንበር ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ሴናተር ጀምስ ኢንሆፌነረ በበኩላቸው፣ የተሰጠው ማብራሪያ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለመረዳት እንዳስቻላቸው መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው ተግባራት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡