ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በአውሮፓዊያኑ 2022 የሚካሄደውን 2ኛውን የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባዔን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ፎረም ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭን ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም እ.ኤ.አ በ2022 የሚካሄደውን የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅትን የተመለከተ እንደነበር ተገልጿል።
አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ስለጽ/ቤታቸው ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የአፍሪካና ሩሲያ ኩባንያዎች በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል የኢኮኖሚ ትብብር ማህበር መቋቋሙን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አያይዘውም ጉባኤው ዝግጅት አካል የሆነ ውይይት በመጪው ክረምት ከአፍሪካ ህብረትና ከአፍሪካ አገራት ጋር ምክክር እንደሚደረግም ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ፍላጎት ለአምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ገልጸውላቸዋል።
ሩሲያ ይህንን መድረክ ለመፍጠር የወሰደችውን ተነሳሽነት አድንቀው፣ ሁለተኛውን የአፍሪካ ሩሲያ ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ፍላጎት እንደላት ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሁለቱ አገራት መካከል በደህንነት፣ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ በግብርና፣ በኢነርጂ፣ በጤና እና በስነ-ምድር ምርምር ዘርፎች ያላቸውን ትብብር በተመለከተ ምክክር አድርገዋል።
አምባሳደር ኦሌግ ኦዜሮቭ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሩስያ ጉብኝት እንዲያደርጉ የሩስያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ የላኩትን ግብዣ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።