ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም የመምራትን ሃላፊነት ተቀበለች

ቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም
ቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም

የካቲት 22/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በቀጠናዊ የሚኒስትሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረምን የመምራት ኃላፊነትን ከኬኒያ መረከቧ ተገለጸ፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል ከኬንያ የሰራተኛና ማህበራዊ ዋስትና ሚኒስትር ሲሞን ቼሉጉዊ ጋር ገንቢ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ሚኒስትሯ የሰራተኞች ፍልሰት አስተዳደርን በማሻሻል ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ገንቢ ውይይት ማካሄዳቸውን ገልፀዋል፡፡

ላለፉት ሁለት አመታት በኬንያ የተመራው 11 የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት ቀጠናዊ የሰራተኞች ፍልሰት መማክርት የሚኒስትሮች ፎረም በርካታ ተግባራትን ሲያካሄድ መቆየቱም ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም የመሪነቱን ሚና ለተጫወተው የኬንያ መንግስትና ለፎረሙ አባል ሀገራት ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

በሀገራት የስራ ገበያ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ የሰው ሀይል ለገበያ ማቅረብ የሀገራቱን ኢኮኖሚ ከመደገፉም ባሻገር ዜጎች የሚገባቸውን ክብርና ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል፡፡

በቀጠናዊ የሚኒስቴሮች ፎረም ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የሚኒስትሮች ፎረሙን የመምራት ሀላፊነት ኢትዮጵያ መቀበሏን ገልፀው የአመራር ሽግግሩ በቅርቡ ይካሄዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ እንደሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በዚህ ዘርፍም የተሰጣትን የመሪነት ሚና ቀጠናዊ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ትሰራለችም ብለዋል፡፡