ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው – የዩኤንሶም ኃላፊ

ሚያዝያ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ የሶማሊያ ተወካይ እና በመንግስታቱ የሶማሊያ የድጋፍ ተልዕኮ (ዩኤንሶም) ኃላፊ ካትሪዮና ላይንግ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ የሶማሊያ ተወካይ እና በመንግስታቱ የሶማሊያ የድጋፍ ተልዕኮ (ዩኤንሶም) ኃላፊ ካትሪዮና ላይንግ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በኢትዮጵያ እና በተባበሩት መንግስታት መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ታዬ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስቀጠል ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

የዩኤንሶም ኃላፊ ካትሪዮና ላይንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።