ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ዕድገት ያበረከተችው አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑ ተገለፀ

ሐምሌ 23/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ማደግ ብሎም መስፋፋት ያበረከተችው አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑን የጅማ ከተማ ከንቲባ ነጂብ አባራያ አስታወቁ።
በታላቁ ጉዞ ከዒድ እስከ ዒድ መርኃግብር ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዲያስፖራ አባላትን ያሳተፈ ሲምፖዚየም በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ጅማ እና አባጅፋር በኢትዮጵያ እስልምና ታሪክ ውስጥ የነበራቸው ከፍታ ከሀገር ግንባታ ጋር የተዋሃደ፣ ዲፕሎማሲን የተከተለ እና ባህር ተሻግሮ መከታ መሆን የቻለ መሆኑን ከንቲባ ነጂብ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ (ፒኤችዲ) በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት በታላቁ ጉዞ እና ከዒድ እስከ ዒድ መጥተው የሀገርን ትክክለኛ ገፅታ በማየት በውጩ ዓለም ያለውን የተንሻፈፈ ዕይታ በማረም ኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የዒድ እስከ ዒድ ኮሚቴ ስብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሀገር በተፈተነችበት ወቅት በዲጅታል ዲፕሎማሲ ደጀንነት የሀገሩን አቋም ለመላው ዓለም በአደባባይ በማሳወቅ ከፍተኛ ትግል ማድረጉን ታሪክ አይረሳውም ብለዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች የተገኙ ሲሆን በመድረኩ ማጠቃለያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይከናወናል ተብሏል።
አክሊሉ ሲራጅ (ከጅማ)