ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ለመላው አፍሪካ ትልቅ ኩራት መሆኑ ተገለጸ

የጋና ወታደራዊ ልዑክ

ኅዳር 18/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ለአለም ሰላም እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካም ጭምር ትልቅ ኩራት ነው ሲሉ የጋና ወታደራዊ ልዑክ ገለፁ።

ልዑኩ በአብዬ የሚገኘውን የ24ኛ ሞተራይዝድ ሰላም አስከባሪ ሻለቃ የግዳጅ አፈፃፀም ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

የልዑኩ መሪ ኮ/ል ፍራንስስ ሳክ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ምንም እንኳን ጋና በሰላም ማስከበር ተሳትፎ ውስጥ የቆየች ሀገር ብትሆንም ኢትዮጵያ ደግሞ ከጋና በተሻለ ልምድ ያላትና በተባበሩት መንግስታት እውቅናና አድናቆት የተቸራት አገር ናት ብለዋል።

እኛም ያየነው ይህንን ልምዷን ተጠቅማ በቀጣናው ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ በሁለቱ ሱዳኖች ስምምነት መሠረት በብቸኝነት ገብታ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በሚገባ ማረጋገጥ መቻሏን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይሄ ደግሞ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካም ጭምር ኩራት መሆኑን ገልፀዋል።

የሻለቃው የሠራዊት አባላትም በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር እና ተቻችለው በሰላም እንዲኖሩ የሚያደርጉትን ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ግዳጅ ከተደረገልን ገለፃ በተጨማሪ ተዘዋውረን በመጎብኘት ማረጋገጥ ችለናል ብለዋል።

በጉብኝታቸውም ብዙ ልምድና ተሞክሮዎች ማግኘታቸውን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።