ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ድብቅ ሴራ የሚያራምዱ የእርዳታ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ልትወሰድ እንደሚገባ ተገለጸ

ነሀሴ 11/2013 (ዋልታ) – የቀድሞዋ የአውሮፓ ፓርላማ አባል እና በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ የአውሮፓ ኅብረት ልዑክን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል- አና ጎሜዝ፡፡ አና ጎሜዝ በወቅቱ መንግሥት በምርጫው ሂደት ላይ ‹‹ሸፍጥ ሠርቷል›› በማለት አጋልጠዋል፡፡

አና ጎሜዝ የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሏቸው የተደበቁ አጀንዳዎች አጋልጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም የሚንቀሳቀሱ የውጭ ድርጅቶች በአብዛኞቹ ድብቅ አጀንዳቸውን እንደሚያራምዱ ነው የገለጹት፡፡ ድርጅቶቹ ሁልጊዜ የሚከሰቱ አደጋዎች በተቻለ መጠን እንዲባባሱ እንጂ የተሻለ ሁኔታ እንዲመጣ ፍላጎት እንደሌላቸውም ተናግረዋል፡፡

አና ጎሜዝ የምዕራባውያን የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳልተዋጠላቸው እና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን ለማየት በእርግጥ ፍላጎት እንደሌላቸው በቅርቡ ለብዙኃን መገናኛ ተቋማት አብራርተዋል። ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት ያስተዳደረውን የአሸባሪው ሕወሓት አገዛዝ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ወደ ሥልጣን ለማምጣት ከንቱ ድካም እየደከሙ መሆናቸውን አጋልጠዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ለውጥ የማይዋጥላቸውና እና የሽብርተኛው ሕወሓት አምባገነናዊ አገዛዝ ተመልሶ እንዲመጣ የሚያሴሩ በልማት ዕርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ በተለይ የእንግሊዝ ፣ የፈረንሣይ እና የጀርመን ድርጅቶች እንዳሉ ነው አና ጎሜዝ የገለጹት፡፡

አና ጎሜዝ እንዳሉት እነዚህ ድርጅቶች አሁን ያለው ጦርነት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፤ ሽብርተኛው ትህነግ የሚፈጽማቸውን ግፎች ይሸፋፍናሉ፡፡ በዚህ አቋማቸው በአንድ ወቅት ከነዚህ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ምክንያቱም የድርጅቶቹ ኮሚሽነር የመለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ እንደነበሩ በመጥቀስ፡፡ እኚህ ኮሚሽነር እና ወዳጆቻቸው በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎች ያቀረቡትን ሪፖርት ለማደባበስ መሞከራቸውን እና ከታዛቢዎቹ ተቃውሞ እንደቀረበባቸው አና ጎሜዝ አንስተዋል፡፡ አና ጎሜዝ ኢትዮጵያ የእርዳታ ድርጅቶችን ድብቅ አጀንዳዎች ማጋለጥ እና እርምጃ መውሰድ አለባት ባይ ናቸው።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠሟትን ተግዳሮቶች የማሸነፍ ሙሉ አቅም እንዳላት ገልፀዋል ሲል አሚኮ ኢፕድ ጠቅሶ ዘግቧል።