ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ሦስት ሳተላይቶችን ታመጥቃለች.

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ለተለያየ አገልግሎቶች የሚውሉ ሦስት ሳተላይቶችን እንደምታመጥቅ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደገለፁት፤ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ለተለያዩ አግልግሎቶች የሚውሉ ሦስት ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ታቅዷል።

በአሥር ዓመቱ ከሚመጥቁት ሳተላይቶች ውስጥ አንደኛው የኮሚዩንኬሽን እና ብሮድካስት ሲሆን፤ የተቀሩት ሁለቱ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ናቸው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የኮሚዩንኬሽን እና ብሮድካስት ሳተላይት የሚባለው በብሮድካስት ሚዲያዎች ለኢንተርኔት፣ ለስክልና ለኮሚዩንኬሽን አገልግሎት የሚውል ነው። በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ እነዚህን አገልግሎቶች ከውጭ በመከራየት በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች።

ለአብነትም፣ ከብሮድካስቲንግ በዓመት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል። ለቴሌ ኮሚዩንኬሽን ደግሞ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ወጭ ይሆናሉ። ስለዚህ ሳተላይት የመገንባት እቅዱን በተግባር በማረጋገጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ ተገቢ ነው።

ከኮሚዩንኬሽን እና ብሮድካስት ሳተላይት በተጓዳኝ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የሚገነቡ ሲሆን፤ በጥቅሉ በዚህ ዘርፍ የሚደረገው ልማት የህዝባችንን ኑሮ በማሻሻል ገቢውን ከማሳደግ አንጸር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።

አቶ አብዲሳ እንደሚሉት፣ ቴክኖሎጂን ከማሳደግ ጎን ለጎን የሥራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት እና ዘርፉ የራሱ የገቢ ምንጭ ሆኖ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኝ ለማድረግ ይሰራል።

የኢፕድ ዘገባ እንዳመለከተው በዘርፉ የሚደረግ ልማት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የሥራ እድል ለመፍጠር እና በየዘርፉ የታዩ ችግሮችን በስፔስ ሳይንስ ስኬታማ ስራዎችን በመስራት ሀገርን በሁሉም ዘርፍ ለማሳደግ መስራት ነው። በተለይም ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የስፔስ ሳይንስ ዘርፉ የውጪ ምንዛሬ የሚያገኝበትን መንገድ አላማ አድርጎ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ በ2011 ዓ.ም የወጣው ፖሊሲ በግልፅ እስንዳስቀመጠው ዘርፉ በራሱ ኢንዱስትሪ ሆኖ በመውጣት የሥራ እድል ለመፍጠርና በቀጣይ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ ዛሬ ላይ የሚሰራው ስራ እና በስፔስ ሳይንስ ውስጥ የሚኖረው ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

የቴክኖሎጂ አቅምን ከመገንባት አንፃር የሚሰራው ስራም ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መተግበሪያዎችን ወደስራ በማስገባት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።