ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ተጋድሎ ፈተናዎችን በድል እየተሻገረች አሸናፊነቷን ታረጋግጣለች – መኮንኖች

ጥቅምት 16/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ተጋድሎ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት እየተሻገረች አሸናፊነቷን ታረጋግጣለች ሲሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ተናገሩ።

በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚገጥማት የውጭም ይሁን የውስጥ ጠላት ያልተሸነፈችው ኢትዮጵያ እስካሁንም ነፃነቷን አስከብራ የዘለቀች ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

በአድዋና ማይጨው የባዕድ ወራሪን አሸንፎ በማስወጣት ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች፤ የአፍሪካ ብሎም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፈር-ቀዳጅ ስለመሆኗም ታሪክ የሰነደው እውነታ ነው።

አሁንም ቢሆን የሚገጥሟትን ፈተናዎች እያለፈች፤ ጠላቶችን እያሸነፈች በድል አድራጊነት የምትሸጋገር መሆኑን የሚጠራጠር ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የለም።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት መኮንኖች ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት እንዲሁም ለሕዝቦች ሰላም ሲባል ሠራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

“መከላከያ ሰራዊት ማለት ሀገር ፍቅር ሰላም ማለት ነው ያሉት መኮንኖቹ ” ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሰራዊቱ በአስተማማኝ ቁመና ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

“ለሀገሬ እስከ ህይወት መስዋእትነት ድረስ አገለግላለሁ” በማለትም በአጽንዖት ተናግረው በዚህም ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ ነን ሲሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ኃላፊነቱን በመወጣት ለኢትዮጵያ የእድገት ስኬት ባለቤትነቱን በተግባር ማሳየት አለበትም ነው ያሉት።

እንዲሁ ሁሉም በየተሰማራበት ሙያ ሁሉ ስለ ሰላም እና ስለ ሀገር ፍቅር ፤ ስለ አንድነት እና ስለመዋደድ እያስተማረ ሀገሩን የሚወድ ትውልድ ማፍራት መቻል አለበት ሲሉ አመልክተዋል።