ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ እንደምትገኝ የተመዘገበው ውጤት ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

ሰኔ 3/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ እንደምትገኝ የተመዘገበው ውጤት ማሳያ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራ ውጤት ማምጣቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገበው ውጤት ማረጋገጫ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙ ግጭቶች፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ጎርፍ፣ አንበጣና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ተቋቁሞ የ2015 ዓ.ም ኢኮኖሚያዊ እድገት 7.5 በመቶ እንደሚሆን ተመላክቷል ብለዋል።

ከተመዘገበው ውጤት በመነሳት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው አዲስ የታሪክ እጥፋት ላይ እንደምትገኝ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በግንቦት ወር ከፍተኛ አመራሩ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተለያዩ መድረኮች ተካሂደዋል ያሉት ሚኒስትሩ በዚህም ሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተገምግሟል ብለዋል።

የብዝኃ ኢኮኖሚ ትግበራ መካሄዱ የማክሮ መዛባቱን ለማስተከሰከል አስችሏልም ነው የተባለው፡፡

ኢኮኖሚው ብዝኃ አቅጣጫን በመጠቀም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማእድን፣ በቱሪዝም እና በሌሎች መስኮች የተሰራው ስራ በዜጎች ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነውም ተብሏል።

በሌላ በኩል መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የከፈተው የሰላም በር ውጤት እየታየበት ነው የተባለ ሲሆን ከተከፈተው የሰላም በር ውጪ ያፈነገጠ ሲኖር የህግ ማስከበር ስራው ይቀጥላልም ነው የተባለው፡፡

በዚህ ረገድ የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በመስከረም ቸርነት