ኢትዮጵያ በእርዳታ ምክንያት ሉዓላዊነቷን የሚጻረር ተግባር አትቀበልም – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ


ነሀሴ 20/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በእርዳታ ምክንያት ሉዓላዊነቷን የሚጻረር ተግባር ፈፅሞ የማትቀበል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንቱ በተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ክንውኖች ላይ በማተኮር መግለጫ ሰጥተዋል።

መግለጫውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የባለ ፀጋ አገራት አምባሳደሮችና አለም አቀፍ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጉትን ውይይት ጠቅሰዋል።

በዚህም በዋናነት አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና በአፋር ክልሎች እያደረገ ያለውን የሽብር ድርጊት አቶ ደመቀ ማስረደታቸውን ተናግረዋል።

በአሸባሪው ድርጊት በሚሊዮኖች ላይ ተፅዕኖ ማድረሱን፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ላይ የመፈናቀልና የበርካቶች ህይወት እየጠፋ መሆኑንም አብራርተዋል ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።

በውይይቱ ላይ የነበሩት አምባሳደሮችና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓባላት በአሸባሪው ቡድን እየተደረገ ያለውን ድርጊት በማውገዝ ዕርዳታ ለማድረስ እክል እየፈጠረ መሆኑን ለአብነት መጥቀሳቸውን ታውቋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ በእርዳታ ምክንያት ሉዓላዊነቷን የሚጻረር ተግባር ፈፅሞ እንደማትቀበል አቶ ደመቀ ገልጸውላቸዋል ነው ያሉት።

ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት በተለያዩ ምክንያቶች ይዘገያል የሚል ሃሳብ ተነስቶ ለማስተካከል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑም ተመልክቷል።

በቅርቡ በዕርዳታ ድርጅቶች ለተጎጂዎች ተብሎ ወደ ሃገር ውስጥ የገባ የምግብ እህል በአሸባሪዎች እጅ መገኘቱ ተራድኦ ድርጅቶች ራሳቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳምንቱ በሳውዲ አረቢያና በሌሎች ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገር ቤት የማምጣት ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

ከላይኛው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ጋር በፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት ላይ ውይይት ማካሄድ፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለተባበሩት መንግስታትና ለተለያዩ ሃገራት የማስረዳትና ሌሎችም አበይት ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።