ኅዳር 15/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ያላትን የላቀ አስተዋፅኦ ሌሎች ሀገራት ሊቀስሙት እንደሚገባ የጃፓን ዓለም አቀፍ የሰላም ትብብር ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር ጄኔራል ካኖ ታኬሮ ጠቆሙ፡፡
በዳይሬክተር ጄኔራሉ ካኖ ታኬሮ የተመራ ልኡክ ቡድን በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋምን ጎበኝቷል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ካኖ ታኬሮ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተሳትፎ ያላትን የላቀ አስተዋፅኦ ሌሎች ሀገራት ሊቀስሙት እንደሚገባ ገልጸው የጃፓን መንግስት የሚያደርገውን ድግፍ እንደሚቀጥልበት ተናግረዋል፡፡
በጉብኝታቸውም የተማሪዎችን ማረፊያ፣ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የትምህርት አሰጣጥን እና የተማሪዎችን ተሳትፎ ተመልክተው በማሰልጠኛ ተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል፡፡
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማእከል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ ጃፓን የኢትዮጵያን ሰላም ማስከበር ተሳትፎ ለማጠናከር በሚሰሩ የአቅም ግንባታ ስራዎችም በቋሚነት እየደገፈች መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይነትም በማዕከሉ በሚከናወነው የአቅም ግንባታ ስልጠና ጃፓን ድጋፏን እንደምትቀጥል ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በሰላም ማስከበር ማዕከል የዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ተቋም አዛዥ ብ/ጄኔራል ሰብስቤ ዱባ ለልኡካን ቡድኑ የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ተሳትፎና የማዕከሉን ሚና እንዲሁም በማሰልጠኛ ተቋሙ እየተከናወኑ ስላሉ የትምህርትና ስልጠና ስራዎች፣ ውጤቶችና ተግዳሮቶች አብራርተዋል፡፡