ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ ያላት ታሪካዊ ሚና እያደገ መምጣቱን ማሳያ ነው – አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

ግንቦት 19/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏ በዓለም አቀፍ ተቋማት ምስረታ እና በአባልነት ያላት ታሪካዊ ሚና እያደገ መምጣቱን ማሳያ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች ድርጅቶች እንዲመሰረቱ ጉልህ ሚና ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆናንም አንስተዋል።

የብሪክስን ጥምረት መቀላቀሏም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረኮች ያላት ጉልህ ተሳትፎና ሚና እያደገ መምጣቱን ዓቢይ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ካሏት ሊለማ የሚችል እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ፣ እና ሰፊ አምራች ሃይል አኳያ እያደገ በመጣው የደቡብ ደቡብ ትብብር ገንቢ ሚና መጫወት እንደምትችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሩሲያ በህዝብ ለህዝብና በልማት የትብብር መስኮች ታሪካዊ እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የብሪክስ ጥምረትም የሀገራቱን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የጋራ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስቀጠል እንደሚረዳ አብራርተዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራትም በዕድገትና ስልጣኔ፣ በባህልና ቀጣናዊ የልማት ትብብር መስክ ገንቢ የምክክርና ውይይት ባህል እያዳበሩ መሆናቸውን ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ብሪክስ የዓለም ጥቅል ዕድገት 35 ነጥብ 6 በመቶ በመሸፈን የተሻለ የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴ አቅም ያለበት ጥምረት መሆኑንም አመላክተዋል።

የጥምረቱ አባል ሀገራትም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ 58 ነጥብ 9 ትርሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድርሻ እና በህዝብ ብዛትም 45 ከመቶውን በመያዝ ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።

በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በነሐሴ/2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከተማ ባካሄደው 15ኛው የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን የጥምረቱ አባል እንዲሆኑ መወሰኑ ይታወቃል።