ሰኔ 26/2013 (ዋልታ) –ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ታላቅነት እና የራሷ ሥልጣኔ እንዳላት መገንዘብ አለብን ስትል ኬንያ ለፀጥታው ምክር ቤት አስታወቀች።
የምክር ቤቱን አራት ወካይ አፍሪካዊያን ሀገራት የጋራ አቋም ያንፀባረቁት በመንግሥታቱ የኬንያ አምባሳደር ማርቲን ኪማኒይ ለኢትዮጵያ ሉኣላዊነት እና የግዛት አንድነት ክብር አለን ብለዋል፡፡
‹‹እኛ እንደ አፍሪካ ዛሬም ሆነ ነገ በዚህ የሙግት መድረክ ላይ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ዝቅ አድርጎ የሚያጠለሽን አግባብ ፈፅሞ አንቀበልም›› ሲሉም አስምረዋል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያን ባጋጠማት ዓይነት ችግር ተሰቃይተናል፤ ለብሔራዊ እርቅ እና አንድነት የምናደርገው ጉዞ ግን አያጠራጥርም ነው ያሉት፡፡
አክለውም ይህንን ስንል እኛ የምክር ቤቱ አራት ወካይ አፍሪካዊያን ሀገራት የምናጠቃልለው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ያለንን ክብር እና ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ነው ብለዋል።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ለዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም እንዲሁም ብልፅግና አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ከሚያደርጉት ጉዞ ጋር በአጋርነት እንደምንቆምም እናረጋግጣለን›› ሲሉም አምባሳደር ማርቲን ኪማኒይ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡