ኢትዮጵያ እና ሕንድ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

ሐምሌ 21/2013 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ሕንድ በጀማሪ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እና በቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ ተቋማት ድጋፍ፣ በሙያተኞች አቅም ግንባታ እና በሌሎችም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን የትብብር ዘርፎች በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒኤችዲ) በደቡባዊ ሕንድ የሚገኙ የተለያዩ የሕንድ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ተቋማትን በመጎብኘት ከየተቋማቱ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አድርገዋል።

በደቡባዊ ሕንድ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ተቋማት በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን መስኮች ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ምክክር አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በገነባችው እና በቅርቡ በሚመረቀው የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤት ላይ ሕንድ በአካል እና በኦንላይን ድጋፍ የሚያድርጉ የሙያተኞችን ድጋፍ እንደምታቀርብ አሳታውቃለች።

ሕንድ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ምቹ የኢኖቬሽን ከባቢ ሁኔታ የመፍጠር ሥራን እንደምትደግፍም አስታውቃለች።

ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒኤችዲ) ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ከሕንድ ጋር በሰጥቶ መቀበል መርሕ በትብብር መሥራት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

የሕንድ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚሰማሩ አልሚዎች ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረች መሆኑን ተናገረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው በሕንድ በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ ሀገራት ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው መስኮች ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ጋር መምከራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።