ኢትዮጵያ እና ቱርክ በወንጀል ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ መንግሥት እና በቱርክ መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚደረገው የጋራ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቱርክ በሽብርተኛ ቡድኖች የደረሰባትን አሳዛኝ ጉዳቶች ኢትዮጵያ እንደምትገነዘብ እና ሽብርተኞችን እንደምታወግዝ እንዲሁም ሽብርተኝነት እንዳይስፋፋ ጠንክራ እንደምትሰራም ገልጸዋል፡፡
የቱርክ መንግሥት የፍትህ ምክትል ሚኒስትር ያኩፕ ሞጉል በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል የተለያዩ ትብብሮች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተው የፍትህ ትብብሮች ሰነድ መፈረማቸው ግንኙነቱን የበለጠ ሕጋዊ መሰረት የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሚፈለጉ ወንጀለኞችም በማንኛውም ጊዜ በፍጥነት ተላልፈው መሰጠት አለባቸው ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ከበርካታ ሀገራት ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራች ሲሆን በፍትህ ትብብሮቹ አስፈላጊና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!