ኢትዮጵያ እና ቻድ በአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

መስከረም 20/2015 (ዋልታ) በካናዳ ሞንትሪያል እየተካሄደ ከሚገኘው 41ኛው የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ጉባኤ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ እና ቻድ በአቪዬሽን ዘርፍ የበለጠ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

በፊርማ ስነስርአቱ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ከቻድ የሲቪል አቪዬሽን እና የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ሚኒስትር ሁሴን ጣሂር ሱጉሜ ጋር በሁለትዮሽ የአቪዬሽን አገልግሎት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ስምምነቱ በአቪዬሽን ዘርፍ በኢትዮጵያ እና ቻድ መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንገድ የሚከፍት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በስምምነቱ ወቅት የቻድ የሲቪል አቬዬሽን እና የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ሚኒስትሩ እንዳሉት እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅጽ ጉባኤ ከ193 አባል ሀገራት ውስጥ የላቀ አፈፃፀም ካስመዘገቡ 5 ሃገራት መካከል አንዷ ከሆነችው ኢትዮጰያ ጋር በአየር ትራንስፖርት ቁጥጥር እና በደህንነት ስርዓቶች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት በበኩላቸው ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን የቆየ ግንኙነት እያጠናከሩ እንደሚገኙ ገልፀው ኢትዮጵያ በአቬይሽን ዘርፍ ያላትን ውጤታማ አፈፃፀምና ልምዶቿን ለማጋራት ቁርጠኛ ነች ማለታቸውን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር  መረጃ ያመላክታል፡፡

 

ቀደም ሲል ኢትዮጵያና ቱርክ በአቬዬሽን ባለስልጣኖቻቸው በኩል ከኢስታንቡል አዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ኢስታንቡል የመሸከም አቅማቸው ከፍተኛ በሆኑ አውሮፕላኖች በረራ ለማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡