ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) – በኢትዮጵያ እና እስራኤል መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ፡፡
በቴል አቪቭ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከእስራኤል የላኪዎች እና ዓለም አቀፍ ንግድ ትብብር ተቋም ጋር በመተባበር በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ በተቋሙ አዳራሽ የክብ ጠርጴዛ ምክክር አድርጓል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶች፣ በኢትዮጵያ በግል ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ኩባንያዎች ባለቤቶችና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
የተቋሙ ምክትል ኃላፊ ሳቢን ሴጋል መድረኩ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች በሥራቸው ዙሪያ የሚያነሷቸውን ችግሮች በጋራ ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው በመጠቆም ምስጋና አቅርበዋል።
በእስራኤል የኢትዮጵያ ልዩ መልክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ÷ በሀገራችን ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና የቱሪዝም አማራጮችን በሚመለከት ሰፊ ገለጻ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ÷ ይህ ትስስር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንስትመንት ለማጠናከር ምቹ አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።
የተቋሙ የዓለም አቀፍ የቢዝነስ ጉዳዮች ኃላፊ ሚስ ሳቢን ሴጋል በበኩላቸው÷ በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል የሚደረገው የኢኮኖሚ ትብብር ከፍተኛ መሻሻልን እያሳየ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም በባለሃብቶቹ የሚነሱ ችግሮችን በጋራ መፍትሄ በመስጠት፣ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የቢዝነስ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶት ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያላት ሀገር መሆኗን አውስተዋል፡፡
በጀመሩት ሥራ ውጤታማ መሆናቸውን የጠቀሱት ባሃብቶቹ በአንዳንድ ምክንያቶች እየገጠማቸው ያለውን ተግዳሮት አስረድተዋል።
አምባሳደር ረታ መንግስት በኢንቨስተሮች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በመዋቅር በሕግ እና በአሰራር ሁኔታዎችን ለማሻሻል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በማስረዳት መፍትሄ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በተለየ ሁኔታ በርካታ የኢኮኖሚና የሕግ ማሻሻያዎች የተደረጉ መሆኑን፣ በተለይ ትኩረት በተሰጣቸው ዘርፎች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታትና አሠራሩን የተሻለ ለማድረግ የወጡትን ሕጎች በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡
ኤምባሲው ችግሮቹን ለመቅረፍ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከኤምባሲው የትኩረት አቅጣጫዎች አንዱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማሳደግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ኤምባሲው የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡