ኢትዮጵያ እና ኮሞሮስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

ሚያዝያ 17/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ኮሞሮስ በመካከላቸው ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአራት የአፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቀጠል ዛሬ ኮሞሮስ መዲና ሜሮኒ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት አዛሊ ጋር ባደረጉት ውይይት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አተገባበር ላይ ገለፃ አድርገዋል።

የወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር የሆኑት የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት አዛሊ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የመሪነት ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ፕሬዝዳንት አዛሊ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም በመስፈኑ መደሰታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የሁለትዮሽ ትብብሩ በግብርና እና አሳ ልማት መስኮች መጠናከር እንደሚችል ያመላከቱት ፕሬዝዳንቱ በህዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንናና ግብፅ መካከል የሦስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል፡፡

የሱዳን የፀጥታ ሁኔታ በውይይት እንዲፈታም ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድን መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ ማድረሳቸውም ተገልጿል፡፡