ኢትዮጵያ ከዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ብዙ እንደምታተርፍ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ከዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ብዙ እንደምታተርፍ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነት እና ድርድር ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይሬክተር አቶ ልሳነወርቅ ጎርፉ  የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ድርድር ሂደት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ  እንደገለፁት ኢትዮጵያ ከዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የተረጋገጠና አስተማማኝ የገበያ ዕድል ማግኘት ትችላለች፡፡

የድርጅቱን የግጭት መፍቻ ስርዓት በመጠቀም በተለይም የእርሻ ወጪ ንግዷ ኢ-ፍትሃዊ ባልሆኑ የውጭ ንግድ እንቅፋቶች በቀላሉ ጉዳት እንዳይደርስበት ለመከላከል እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

የህጎች ግልጽነትና አስተማማኝነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ስላለው ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት መስፋፋት አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ጠንካራ መልዕክት በማስተላለፍ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የሚያበረታታ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ልሳነወርቅ በተለይም ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት ሀገር በመሆኗ በወጪና ገቢ ንግድ ረገድ የትራንዚት መብቶችን እንድታገኝና ተጠቃሚ እድትሆን የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአለም ንግድ ድርጅት ምንነትና አባልነት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በአግባቡ ከመረዳትና ለሌሎች ከማስረዳት ጎን ለጎን መስራት የሚጠበቅበትንና ዘርፉ የሚጠይቀውን ሀገራዊ ተልዕኮ በመወጣት ኢትዮጵያ የአለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያደረገች ያለው ድርድር ይሳካ ዘንድ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ሲሉ አቶ ልሳነወርቅ ማሳሰባቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር  ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡