ኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ ላይ ናት – ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ


ሐምሌ 15/2013 (ዋልታ) – የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ በባህርዳር የአንድ ጀበር የ247 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አስጀምረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ የህልውና ዘመቻ ነው ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያን የነፃነት ታሪኳን ለማደብዘዝ ከውጭና ከውስጥ ጥንት ጠላቶቻችን ጋር በመሆን የህልውና አደጋ ላይ ለመጣል እየተጉ በመሆኑ እኛም ህልውናችንን ለማስጠበቅ ወደ ዘመቻ ገብተናል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢኮኖሚ ለማደግ የተፈጥሮ ሀብታችን የሆነውን አባይን ገድብን እንዳንጠቀም ለማድረክ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም በጥረታችን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ማሳካት ችለናል ብለዋል ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ።
አባይን ከደለል ለመታደግና የተፋሰስ ልማታተችን ማጠናከር አለብን ያሉት ም/ርዕሰ መስተዳደሩ መከላከያ፣ ልዩ ኃይልና ሚኒሻው ለሀገር ህልውና ደሙን እያፈሰሰ እኛ ደግሞ በልማት በኢኮኖሚ ለማደግ የምናደርገውን ጥረት ሌት ከቀን መስራት ይገባል ብለዋል።
በአማራ ክልል ባለፈው አመት በአንድ ቀን 190 ሚሊየን ችግኝ ተተክሎ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በዛሬው እለትም በአንድ ጀምበር በ24 ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ በ157 ወረዳዎች 247 ነጥብ 8 ሚሊየን ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ኃላፊ ዶ/ር መለሰ መኮንን ገልፀዋል።
አባይ አልምተን እንዳንጠቀም የሚሹ ሀይሎች ኢትዮጵያን በውክልና ውክልና ጦርነት ውስጥ ሊያስገቡ በመጣር ላይ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ በዚህ አመት በ185 ሺህ ሄክታር መሬት ከሚተከለው 2 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሚሆነው በአባይ ተፋሰስ ውስጥ በሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች መሆኑም ተገልጿል።
በባህርዳር ቤዛዊት ተራራ ላይ የአንድ ጀበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የሃይማኖት መሪዎች ፣ታዋቂ አርቲስቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በአማራ ክልል 3ኛው አረንጓዴ አሻራ በሃገር ደረጃ 6 ቢሊዮን በክልል ደረጃ ደግሞ 2 ቢሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃግብር በጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡
(በምንይሉ ደስይበለው)