ሐምሌ 1/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ኅብረት 2022ን የሥርዓተ ምግብ እና የምግብ ዋስትና ዓመት እንዲሆን ይፋ ባደረገው መሰረት ኢትዮጵያም የሥርዓተ ምግብ እና የምግብ ዋስትና ዓመትን ይፋ አድርጋለች።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በመርኃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ የሥርዓተ ምግብ እና የምግብ ዋስትና ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ያለውን ቁርጠኝነት ለማጎልበት እና በአፍሪካ ሀገራት መካከል የእውቀት ልውውጥ ለማካሄድ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
የኅብረቱ አባላት እና ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ተግባር እንዲያከናውኑ በማበረታታት በጋራ በመሆን ለአፍሪካ አዎንታዊ የሆነ የሥርዓተ ምግብ እድገትን መፍጠር እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ፒኤችዲ) በበኩላቸው የአፍሪካ ኅብረት የምግብና የምግብ ዋስትና ዓመት እንዲሆን ወስኖ ይፋ መደረጉ “በአፍሪካ አኅጉር የተመጣጠነ አመጋገብ እና የምግብ ዋስትና አቅምን፣ የግብርና ውጤት የሆኑ ምግብ ሥርዓቶችን፣ ጤና እና ማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓቶችን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ኅብረት አመራሮች፣ ሚኒስትሮች እና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የአጋር ድርጅቶች ኃላፊዎች እና ለጋሾች፣ በፌዴራል ደረጃ የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች መገኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW