ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ችግሮች በአፍሪካዊያን እንደሚፈቱ የጸና እምነት አላት – አምባሳደር ተሾመ ቶጋ

መስከረም 4/2015 (ዋልታ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በቤጂንግ ላሉ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባላት እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ተለዋጭ አባል በመሆን እያገለገሉ ለሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት (A3) አምባሳደሮች በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አምባሳደሩ በአሸባሪው ህወሃት አማካኝነት የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ኢትዮጵያ ከመነሻው ጀምሮ የሄደችበትን ርቀት በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን መንግስት ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስምረውበታል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ችግሮች በአፍሪካዊያን እንደሚፈቱ የጸና እምነት አላት ያሉ ሲሆን በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ለሚደረገው የሰላም ድርድር ሂደት የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አፍሪካውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነትና በትብብር ከሰራን የሚያጋጥሙንን ችግሮች በቀላሉ መቅረፍ እንችላለን ማለታቸውን የኤምባሲው መረጃ ያሳያል፡፡

አምባሳደሮቹ ስለጉዳዩ ከሚዲያና ከተለያዩ አካልት ከሚሰሙት ይልቅ በኤምባሲው በኩል በቀጥታ ማብራሪያ ስለተሰጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑንና ለዚህም ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ የገለጹ ሲሆን ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለው መርህ ወሳኝ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡