ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት መስጠቷን አጠናክራ ትቀጥላለች – ዶ/ር ሊያ ታደሰ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ መስጠት የጀመረችውን የኮቪድ-19 ክትባት አጠናክራ እንደምትቀጥል ጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

ክትባቱን የጀመሩ አገራት አጋጠመን ባሉት ተጓዳኝ ጉዳት ለጊዜው ክትባቱን ማቆማቸው ቢሰማም ኢትዮጵያ የክትባቱን ተጓዳኝ ምልክት እያጠናች መከተቧን እንደምትቀጥል የጤና ሚኒስትሯ በሰጡት መገለጫ ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል ደረጃ የተጀመረው የክትባት መርሀ ግብር እስካሁን በ10 ክልሎችና ሁለት ከተማ መስተዳድሮች እየተሰጠ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ሊያ፣ አሁንም ለጤና ባለሙያዎች፣ እድሚያቸው ከ65 በላይ ለሆኑና ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች መሰጠቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የአስትራ ዜኒካን ክትባት የጀመሩ ሀገራት ክትባቱን በሚወስዱ ሰዎች ላይ ባጋጠመ የደም መርጋት እክል ለጊዜው ክትባት መስጠት አቁመዋል ከመባሉ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ጉዳዩ ስላላጋጠመ የተጀመረው ክትባት እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

አሁን ላይ ክትባቱን እንዳቆሙ ያስታወቁት አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት እስካሁን ከ11 ሚሊየን በላይ ዜጎችን እንደከተቡና ከዛ ውስጥም ክትባቱ 20 ሰዎች ላይ የተለየ ተጓዳኝ ችግር እንዳሳየ ነው በመረጃው የተጠቀሰው።

ኮሮና ኢትዮጵያ ከገባ አንድ አመት የሞላው ሲሆን፣ በአንድ አመት ውስጥ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል በተሰራው ርብርብ ቫይረሱ ሊያደርስ ከሚችለው ኪሳራ አንፃር ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ እንደተቻለ ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙና ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ እንዳሳየም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ባለፉት ሳምንታት በቫይረሱ የሚያዙና ህይወታቸውን የሚያጡ ዜጎች ቁጥር መጨመር ያሳሰበው የጤና ሚኒስቴር፣ አሁንም መዘናጋትና ቸልተኝነት እንደማያስፈልግና የኮቪድ-19 መከላከያ ደንቦችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

መጋቢት 4 በአገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19ኝን ክትባት የጀመረችው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ክትባቱን ካገኙ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡

(በደምሰው በነበሩ)