ኢትዮጵያ የዓለም አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ሆነች

ሐምሌ 10/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል የዓለም አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባል ሆና እንድታገልገል በአፍሪካ ኅብረት ተመርጣለች።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በዛምቢያ ሉሳካ በተካሄደው የኅብረቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።

የአስፈፃሚ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ኅብረት የ2023 በጀት 654 ነጥብ 8 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ማጽደቁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበጀት ማፅደቁ ሂደት ለሰላም ማስከበር የሚውለው በጀት ሙሉ በሙሉ በዓለም ዐቀፍ አጋሮች እንዲሸፈን መደረጉ አግባብ አለመሆኑን አንስተዋል።

ለተመሰረተው የአፍሪካ መድኃኒቶች ኤጀንሲ ዋና መቀመጫ አስተናገጅ ሀገር ለመምረጥ በተያዘ አጀንዳ በመወዳደሪያ መስፈርት አጣርቶ ሩዋንዳ ከአልጄሪያ እና ቱኒዚያን ጋር ተወዳድራ ተመርጣለች።

መደበኛ ስብሰባው የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል (Africa CDC) ራሱን ችሎ ሙሉ ስልጣንም እንዲኖረው የመመስረቻ ሰነዱ ላይ የቀረበውን ረቂቅ ማሻሻያ አፅድቋል።